Amharic Bible

ትንቢተ ሚክያስ
Chapter 1 of 7
left-arrow Chapter - 1 right-arrow
Verse 1

በይሁዳ ነገሥታት በኢዮአታምና በአካዝ በሕዝቅያስም ዘመን ወደ ሞሬታዊው ወደ ሚክያስ የመጣው፥ ስለ ሰማርያና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው፥ የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው።

Verse 2

እናንተ አሕዛብ ሁሉ፥ ስሙ፤ ምድርም ሙላዋም ታድምጥ፤ ጌታ እግዚአብሔርም፥ እርሱም በቅዱስ መቅደሱ የሆነ ጌታ፥ ይመስክርባችሁ።

Verse 3

እነሆ፥ እግዚአብሔር ከስፍራው ይወጣል፥ ወርዶም በምድር ከፍታዎች ላይ ይረግጣል።

Verse 4

ተራሮችም በእሳት ፊት እንዳለ ሰም፥ በገደልም ወርዶ እንደሚፈስስ ውኃ፥ በበታቹ ይቀልጣሉ፥ ሸለቆችም ይሰነጠቃሉ።

Verse 5

ይህ ሁሉ ስለ ያዕቆብ በደልና ስለ እስራኤል ቤት ኃጢአት ነው። የያዕቆብም በደል ምንድር ነው? ሰማርያ አይደለችምን? የይሁዳስ የኮረብታው መስገጃ ምንድር ነው? ኢየሩሳሌም አይደለችምን?

Verse 6

ስለዚህ ሰማርያን በሜዳ እንደሚገኝ የድንጋይ ክምር፥ ወይን እንደሚተከልበትም ስፍራ አደርጋታለሁ፤ ድንጋዮችዋንም ወደ ሸለቆ እወረውራለሁ፥ መሠረቶችዋንም እገልጣለሁ።

Verse 7

የተቀረጹትም ምስሎችዋ ይደቅቃሉ፥ በግልሙትና ያገኘችው ዋጋ ሁሉ በእሳት ይቃጠላል፥ ጣዖታትዋንም ሁሉ አጠፋለሁ፤ በግልሙትና ዋጋ ሰበሰበቻቸው፥ ወደ ግልሙትናም ዋጋ ይመለሳሉና።

Verse 8

ስለዚህ ነገር ዋይ ብላ ታለቅሳለች፥ ባዶ እግርዋንና ዕራቁትዋን ሆና ትሄዳለች፤ እንደ ቀበሮ ታለቅሳለች፥ እንደ ሰጐንም ዋይ ትላለች፤

Verse 9

ቍስልዋ የማይፈወስ ነውና፤ እስከ ይሁዳም ደርሶአልና፥ ወደ ሕዝቤም በር ወደ ኢየሩሳሌም ቀርቦአልና።

Verse 10

በጌት ላይ አታውሩ፤ በአኮ ላይ እንባን አታድርጉ፤ በቤትዓፍራ በትቢያ ላይ ተንከባለሉ።

Verse 11

በሻፊር የምትቀመጪ ሆይ፥ በዕራቁትነትሽና በእፍረት እለፊ፤ በጸዓናን የምትቀመጠው አልወጣችም፤ የቤትኤጼል ልቅሶ ከእናንተ ዘንድ መኖሪያውን ይወስዳል።

Verse 12

ክፉ ነገር ከእግዚአብሔር ዘንድ እስከ ኢየሩሳሌም በር ድረስ ወርዶአልና በማሮት የምትቀመጠው በጎነትን ትጠባበቃለች።

Verse 13

በለኪሶ የምትቀመጪ ሆይ፥ ሰረገላውን ለፈረስ እሰሪ፤ እርስዋ ለጽዮን ሴት ልጅ የኃጢአት መጀመሪያ ነበረች፤ የእስራኤል በደል በአንቺ ዘንድ ተገኝቶአልና።

Verse 14

ስለዚህ ትሎት ለሞሬሼትጌት ትሰጪአለሽ፤ የአክዚብ ቤቶች ለእስራኤል ነገሥታት አታላይ ይሆናሉ።

Verse 15

በመሪሳ የምትቀመጪ ሆይ፥ ወራሽ አመጣብሻለሁ፤ የእስራኤል ክብር ወደ ዓዶላም ይመጣል።

Verse 16

ተማርከው ከአንቺ ዘንድ ወጥተዋልና ስለ ተድላሽ ልጆች ራስሽን ንጪ፥ ጠጕርሽንም ተቈረጪ፤ ቡሃነትሽንም እንደ ንስር አስፊ።

Chapter -
1